ህወሃት ኢህአዴግ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል በሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶች ወደ ሰሜን ጎንደር እያንቀሳቀሰ ነው

ግንቦት ፳፰ ( ሃያ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን በሰሜን ጎንደር በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ አውደ ውጊያዎች ተደጋጋሚ ሽንፈትን ያስተናገደው ገዥው ህወሃት ኢህአዴግ ተጨማሪ ወታደሮችን በሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶች በመጫን ማጓጓዙን ቀጥሏል። ምንጮች እንዳሉት ወታደሮችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች በሚያርፉበት ወቅት እንዳያስታዋሉት አብዛሃኞቹ እድሜያቸው ለአቅመአዳም ያልደረሱ በግምት ከ17 ዓመት በታች የሚሆናቸው ለጋ ወጣቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል። እነዚህ አዲስ ምልምል ወታደሮች ከወታደራዊ ትጥቅ ውጪ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ አለመያዛቸውንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
ወታደሮችን በኮንቮይነት የማጀብ ሥራው በፖሊስ ሰራዊት እና በደህነት ሃይሎች እየተከናወነ ነው። በሰሜን ጎንደር ዳባት፣ አጅሬ፤ ጃኖራ አካቢቢዎች ከተለያዩ የጦር ክፍሎች ተውጣጠው የተላኩ የስርዓቱ ወታደሮች ከፍተኛ የሆነ ተደጋጋሚ ሽንፈትን አስተናግደዋል። ከአሳፍሪው ሽንፈት በኋላ የስርዓቱ ወታደራዊ ባለስልጣናት የአካባቢው ነዋሪ ለአርበኞች ግንቦት ሰባት እና ለነጻነት ታጋዮች በሚያሳየው ወገንተኝነት ተደናግጠዋል። በከፍተኛ የጦር መሳሪያዎች የታገዘ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ በማድረግ የነዋሪውን ሕዝብ ስነልቦና ለማሸበር ያደረጉት ጥረት አልተሳካም።
ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም ምሽት ላይ የዓርበኞች ግንቦት ሰባት ወታደራዊ ክንፍ በወሰደው የማጥቃት እርምጃዎች የህወሃት መራሹ ጦር ክፉኛ ጉዳት እንደደረሰበት ንቅናቄው ማስታወቁ ይታወሳል። በህወሃት ኢህአዴግ በኩል ሰሞኑን ስላጋጠመው ሽንፈትም ይሁን ጥቃቶች ምንም ዓይነት መግለጫ አልተሰጠም።