ህወሃት በአገሪቱ ለሚታየው ችግርና ለኢህአዴግ ውድቀት ብአዴንን ተጠያቂ አደረገ። የብአዴን አመራሮች የክልሉ ጸጥታ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ነው በማለት ተናግረዋል።

ሐምሌ ፲፰ ( አሥራ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ብአዴን የክልል አመራሮችን፣ ሁሉም የቢሮ ምክትል ኃላፊዎችን እንዲሁም በጥንቃቄ የመረጣቸውን አባሎቹንና አገዛዙን የደግፋሉ ያላቸውን የሃገር ሽማግሌዎች ቡድን ይዞ መቀሌ ቢሰነበትም፣ ያገኘው መልስ ወቀሳና ተጠያቂነትን ያዘለ ትችት ብቻ እንደነበር ምንጮች ይገልጻሉ። ብአዴንና ህወሃት የህዝብ ለህዝብ ፣ የከፍተኛ አመራሮች እና የሁለቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ብቻ የተገኙበትን “ሶስትዮሽ” የተባለውን ውይይት አድርገዋል። በከፈተኛ አመራሩ መካከል በተደረገው ስብሰባ ህወሃት “የብአዴን አባላት ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ እና ለስርዓቱ ስጋት የሆኑትም የብአዴን አባላት” ናቸው ሲሉ ወቀሳ አቅርበዋል።
ብአዴን አባላቱን እንዲያጠራ ያስጠነቀቁት የቀድሞው የህወሃት መስራች አቶ ስብሃት ነጋ፣ የአባላት ማጥራት ሂደቱ በፍጥነት መጀመር እንዳለበት እና ይህ ካልሆነ ግን ሀገሪቱ በሁለቱ ክልሎች ችግር ወደ ማትመለስበት አዝቅት ልትገባ እንደምትችል ተናግረዋል። “ ኢህአደግ የተፈተነበት እና የሚፈተነበት ወቅት ላይ ነው” ያሉት አቶ ስብሃት፣ ኃላፊነቱን የሚወስዱት ብአዴን እና ኢህአዴግ ናቸው ብለዋል፡፡
“የወልቃይት ጥያቄ የህወሃት አጀንዳ እንጅ የብአዴን እና የአማራ ህዝብ ሊሆን እንደማይችል” የተናገሩት አቶ አባይ ወልዱ፣ ይህም በምንም ህዝበ ውሳኔ እና የምርጫ አማራጮች እና የማንነት ጥያቄ የሚያስተናግድበት ምንም አይነት ወቅታዊ እቅድም ሆነ ሃሳብ እንደሌለው በመጥቅስ፣ የብአዴን አመራሮች በተቃዋሚነት የመነጠቅ እና በዲያስፖራው ሃሳብ የመመራት አባዜ እንዲያቆሙ አሳስበዋል። ፓርቲው አዲስ ስትራቴጅ መቀየስ እንደላበትም ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ባደረጉት ስብሰባ ላይ አብዛኞች የመከላከያ ጀኔራሎች መገኝታቸው አንዳንድ የብአዴን አመራሮችን አስከፍቷል። ህወሃት ጄኔራሎችን ደርድሮ ያሳየን ወታደራዊ የበላይነቱን ሊያሳየን ፈልጎ ነው ሲሉ ተችተውታል። በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ይደረጋል የተባለው ውይይት ወደ ትእዛዝ አምርቶ፣ ህወሃት ማስፈራሪያውን ሲያዥጎደጉድና የብአዴን አመራሮችም የረባ ነገር ሳይናገሩ ተጠናቋል፡፡ አጠቃላይ ስብሰባው ብአዴን ይበልጥ ወደ ጎን እንዲሸሽ ያደረገ ፤ መከላከያው በትግራይ እጅ መሆኑን ያሳየ እና ያሳሰበ ነበር ሲሉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡በስነ ስርዓቱ ላይ “በመስከረም ጎንደር ላይ ደግሰን እንጠብቃችኃለን” ከማለት ያለፈ ምንም ያልተናገሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የብአዴንን አቋም በፓርቲዎች ውይይት ላይ ሳያቀርቡ ቀርተዋል።
በሌላ በኩል የክልሉ ሰላም ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ መጥቷል ሲል ብአዴን በዝግ በመከረበት ስብሰባ ላይ ገልጿል።
አቶ አለምነው መኮንን ሙሉ ቀንና እስከ ምሽቱ 3 ሰአት በመሩት የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ላይ የባህር ዳር ወቅታዊ ሁኔታ በአስጊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና ማንኛውም ወደ ክልሉ ርዕሰ ከተማ የሚመጡ እንግዶች አቅጣጫ እየቀሩ እና ካደሩም የማይሰነበቱባት ከተማ እየሆነች መጥታለች ብለዋል።
“በቀን አንድ ሰው እየታረደ እና እየተገደለባት የምትገኝው ይህች ከተማ”፣ ነጋዴዎች፣ አውሮፓ ሆነው በሚመሩ ሚዲያዎች እና ማህበራዊ ገፆች ትዕዛዝ የሚያድሩበት ፣ የሚመገቡበት እና የሚዝናኑበት ቦታ ሁሉ የተወሰነበት እና የከተማዋ ሰላም በመሳሪያ በሚደገፍ አመፅ እየታመሰ ፣ በከተማዋ የሚገኙ የንግድ ከተሞች እዳቸውን ለመክፈል ባለመቻላቸው ሆቴላቸውን እንድንረከባቸው እየጠየቁ ነው ብለዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ለብአዴን አመራሮች አራት የመነሻ ጥያቄዎች በአቶ አለም ነው የተሰነዘሩ ሲሆን ፤ አሁን ያለው ሁኔታ አንድምታው ምንድን ነው፣ የከተማዋ እጣ ፈንታስ ወደፊት ምን ይሆናል ፣ የችግሩ ምክንያት ምንድን ነው፣ ሌሎች ወደ ነበሩበት ሲመለሱ ባህር ዳር ለምን ሳትመለስ እንዳመፀች ቀረች እና የመፍትሄ አቅጣጫውስ ምንድን ነው የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
በውይይቱ “አመራሩ ችግር ፈጣሪዎችን በአደረጃጀት በመለየት እና ህዝባዊ ጥናት አካሂዶ የችግሩን ተዋናዮች መቆጣጠር አልቻለም” ተብሏል፡፡
“ጎንደር ኃምሌ አምስት ቀን ህዝባዊ አመፅ ተጠብቆ እያለ በተሰራው የመንደር አደረጃጀት የተፈራው ግዙፍ ሰልፍ ወደ መሰረተ ልማት ጉብኝት ተቀይሮ በደስታ በረካንበት ፤ በጎንደር እና ባህር ዳር ፣ ደሴ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን መሰረት ባጠፋንበት በዚህ ሰዓት ደህንነታችን እና ሰላማችንን ለማስጠበቅ የሚያስችል ሁኔታ ላይ አለመሆናችንን ግን ባህር ዳር እያስመሰከረች ነው፡፡ ከምሽቱ አንድ ስዓት ጀምሮ በጎዳናዎች ሰዎች የሚጠፉባት፣ በቀን የአንድ ወይም የሁለት ሰዎች ህይዎት የሚጠፋባት፣ ገዳዮች አንድም ቀን የማይያዙባት ከተማ ሁናለች” ያሉት የክልሉ በአዴን ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የአሜሪካ መንግስት ዜጎቹ ላይ የጉዞ እገዳ ያላነሳው ለባህር ዳር ከተማ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
ባህር ዳር የፀረ ሰላም ኃይሎች ምርኮኛ ሁናለች የሚሉት አቶ አለምነው፣ “ በህዋስ እንደገና ውይይት እንዲካሄድ፣በሰፈር አደረጃጀት እንዲፈጠር ፣ መሰረታዊ ድርጅት በቋሚነት ክትትል እንዲያደርግ ፣የትኛው ሰፈር ለውጥ አመጣ እያለ እንዲገመግም አቅጣጫ አስቀምጠዋል። የ2008 ዓ.ም ህዝባዊ አመፅ በብአዴን ታሪክ ፈታኝ ወቅት፣ የማይረሳ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ክስተት ዘመን ነው የሚሉት አቶ አለምነው፣ ምንም ጠንካራ ተቃዋሚ ሳይኖር ከ404 ሚሊየን ብር በላይ ንብረት ያወደመ ክስተት በባህር ዳር እና ጎንደር መከሰቱንም አመላክተዋል።
የብአዴን አመራሩ ባካሄደው ውይይት ሰው ቤት ውስጥ እና ከውጭ የሚገደልባት ፣ ቦምብ ሰው በተሰበሰበበት የሚወረወርባት ፣ አመፂያኖች የማይያዙባት ፣ የፍርሃት ድባብ ያልተቀረፈበት ፣ የሰዓት ገደብ ሳኖር ህዝቡ በራሱ የሰአት ገደብ ያወጣበት መሆኑ በስብሰባው ላይ ተገልጸሏል። እንደማሳያም ጎንደር እስካሁን ስድስት ቦምቦች ተወርውረው ሶስቱ ሲያዙ ፣ ባህር ዳር ግን ሰምንት ጊዜ ተወርውሮ አንዱም ያልተያዘበት እና ለዚህ መሪ ተዋናይ ናቸው ተብለው የሚጠረጡሩት የባጃጅ አሽከርካሪዎች በመንግስት ላይ መንግስት መስርተው ለህዝቡ የአመፅ ጥሪየሚያስተላልፉበት ፣ እና እቅስቃሴውን ከተራ ሻሂ ቅጠል ጀምሮ አግላይ የሆነ የማህበረሰብ እንቅስቃሴ እየመራበት ያለ ሁኔታ መፈጠሩም ተብራርቷል። በዚህም በባጅጅ ማህበራት የኢህአዴግ አደረጃጅት እንዲገባ እና እንዲመራ ማሳሰቢያ አስቀምጧል፡፡