ህወሀት የመለስና የሚስቱ ፓርቲ እየሆነ ነው ተባለ

መጋቢት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአንድነት የአመራር አባል ይህን የተናገሩት አትላንታ ተዘጋጅቶ በነበረው ዝግጅት ላይ ነው።

አቶ ስየ ከተሰብሳቢው ጥያቄ በቀረበላቸው ጊዜ ”  በአጠቃላይ ህወሃት የመስራች ወይም የአባላቱ ፓርቲ አይደለም። እባካችሁ የትግራይም ነው አትበሉ። የቤተሰብ ፓርቲ  እየሆነ ነው። ከዚያም እየቀጠነ የመለስ እና የሚስቱ የአዜብ ፓርቲ እየሆነ ነው ያለው።” በማለት ተናግረዋል።

ኦህዴድ ወይም ብአዴን የሚለው ነገር ምርጫ ለመስረቅ ካልሆነ በቀር፤ የሚያስፈልጉ ድርጅቶች አይደሉም በማለት አቶ ስየ አጣጥለዋቸዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታየው የኑሮ ውድነት ኢህአዴግን ተጠያቂ ያደረጉት አቶ ስየ ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ  “ኢህአዴግ ትልቅ የቢሮክራሲ ተቋማትን ገንብቷል። እነዚህን ተቋማት መመገብና ማቆየት ይኖርበታል። እነዚህ ተቋማት ደግሞ ቀዳዳ በርሜሎች ናቸው። “ዘርፎም፣ ነጥቆም ቢሆን ገንዘብ ከህዝቡ መውሰድ አለበት። ደርግም በመጨረሻም አመታት የሆነው እንደዚህ ነው። ጦርነቱ በተፋፋመ ቁጥር ብዙ ገንዘብ ማፍሰስ አስፈልጎ ነበር። በዚህ ምክንያት ወደፊትም ወደኋላም መሄድ የማይችልበት ደረጃ ላይ ነበር የደረሰው ፣ አሁንም ኢህአዴግ እንደዚህ ነው የሆነው – የማይወጣበት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ብለዋል።

አቶ ስየ  “ይህ የኑሮ ውድነት ምርጫ 97ትን ተከትሎ የመጣ መሆኑን” ጠቅሰው፣ ኢህአዴግ  “የተለያዩ ማህበራትን አደራጅቶ ገንዘብ መርጨት ጀመረ። ይሄ ሲሄድ ሲሄድ 2001 ላይ ከቁጥጥር ውጪ ሆነ። በዚህ በተንሸራተተ ኢኮኖሚ ላይ ሆኖ ነው አቶ መለስ ዜናዊ ትራንስፎርሜሽንን ያወጀው። “ሲሉ አክለዋል።

 “የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድም በድንገት በምርጫ 97 ወዲህ የመጣ ነው ያሉት አቶ ስየ ” ይህም ልማታዊ ባለሃብት ብቻ ሳይሆን ልማታዊ ጋዜጠኛ የሚባል ነገር ፈጥሮብናል።  ኑሮ ተወደደ። ሙስና ተስፋፋ። እና አሁን የትም ቦታ ብትደውሉ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚናገረው ስለችግር፣ ስለ ሙስና፣ ስለኑሮ ውድነት ነው የሚያወራው። ይህ ጥሩ ምልክት አይደለም። አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከዳር የኢኮኖሚ ችግር አጀንዳ እያነሳ ነው። አሁን ያለው ችግር ከስርአቱ ከኢህአዴግ ጋር የተያያዘ፤ ኢህአዴግ ያመጣው መሆኑን ህዝቡ ተገንዝቧል። ስለሆነም የኢኮኖሚው ችግር በመዝባሪው ነጋዴ ብቻ የመጣ ነው ብሎ ለማጭበርበር አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ሁሉም ጣቶች ወደ አገዛዙ ባህሪ እያመለከቱ ናቸው። ይህም አዲስ ክስተት ነው። ጥያቄውም ከኢኮኖሚ ጥያቄ ወደ ፖለቲካዊ ጥያቄ እያመራ ነው።” ማለታቸውን የኢትዮጵያ ሚዲያ ፎረም ዘግቧል።

ስብሰባውን አዘጋጀው የአትላንታ አንድነት ፓርቲ የድጋፍ ኮሚቴ ነው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide