ሁለት ኢትዮጵያውያን በሳውዲ አረቢያ አንገታቸው ተቀልቶ ተገደሉ

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 17/2009)ባራሂ መንገሻና ተወልደ ገብረስላሴ በሪያድ ከተማ ፓኪስታናዊውን የታክሲ ሹፌሩ ራቅ ወዳለ ስፍራ በመወሰድና በጩቤ በማስፈራራት አንገቱን በገመድ አንቀው ከገደሉት በኋላ ከመኪናው ወንበር ጋር አስረውት መሄዳቸውን ነው የሳውዲአረቢያ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ያስታወቀው።

ኢትዮጵያውያኑ የታክሲ ሹፌሩን ከገደሉት በኋላ ገንዘቡን ዘርፈው እኩል መከፋፈላቸውን የሀገሪቱን ባላስልጣናትን ጠቅሶ ሪያድ ዴይሊ ዘግቧል።

ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ወንጀሉን መፈጸማቸውን በማመናቸውና በማስረጃ በመረጋገጡ አንገታቸው ተቀልቶ በሞት እንዲቀጡ መደረጉን ዘገባው አመልክቷል።

ሪያድ ዴይሊ እንደዘገበው በራሂ መንገሻና ተወልደ ገብረስላሴ ላይ የሞት ቅጣቱ የተፈጸመባቸው በሳውዲአረቢያ የሸሪያ ህግ መሰረት ነው።

የሸሪያ ህጉ ማንኛውም ሰው የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ ሲጥልና በስርቆት ምክንያት ሰው ቢገድል አንገቱ ተቀልቶ በሞት እንደሚቀጣ ይደነግጋል።

ስለ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን የሞት ቅጣት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት ያለው ነገር የለም።