ሀብታሞችና የኢህአዴግ አባላት ጭንቀት ውስጥ ናቸው::

ሐምሌ ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-  የአቶ መለስ ዜናዊ የጤና ሁኔታ ተሻሽሎ ከዛሬ ነገ ወደ አገር ይመለሳሉ በማለት ተስፋ አድርገው የነበሩት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች እንዲሁም የኢህአዴግ አባላትና በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ  ባለስልጣናት በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ነው የኢሳት የመንግስት የውስጥ ምንጮች የሚናገሩት።

ባለሀብቶች በየጊዜው ከባለስልጣናት መረጃዎችን ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉ የገለጡት ምንጫችን ፣ መረጃ የሚሰጥ አካል መጥፋቱና በህዝቡ ውስጥ ያለው ውዥንብር ባለሀብቶች ሀብታቸውን ለማሸሽ ዘመቻ ጀምረዋል።

በዚህም የተነሳ በአገሪቱ ያለው አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴ ተዳክሟል። በተለይም በክፍለ ሀገራት ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶች በስጋት ወደ መሀል አገር እየመጡ ነው። አንዳንዶች ገንዘባቸውን ከባንክ እያወጡ፣ ወደ ውጭ አገር ገንዘቦች በመመንዘር እና ለማሸሽ ከፍተኛ ሙከራ እያደረጉ ነው።

በተመሳሳይም በኢህአዴግ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አባላትና የአመራር አባላት መረጃ ለማግኘት አለመቻላቸው ግራ አጋብቶአቸዋል። አብዛኛው የኢህአዴግ አባል መረጃውን የሚሰማው በተለይ ከውጭ አገር የመገናኛ ብዙሀን ሲሆን፣ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናትም የኢሳትን የራዲዮ ስርጭት በሳተላይት ለማስገባት ዲሾችን በብዛት ማስገባታቸውን እና ዜናውን በትኩረት መከታታል መጀመራቸውን ነው ለማወቅ የተቻለው። በውጭ አገር የሚገኙ አንዳንድ ባለሀብቶችና ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ የፈለጉ የውጭ አገር ዜጎች፣ ወደ ኢሳት ጣቢያ በመደወል አዲስ አበባ እንዴት ዋለች በማለት እየጠየቁ ነው።

የአቶ መለስ የጤና ሁኔታ ለኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀር ድብቅ እንዲሆን መደረጉ ግንባሩን እየፈረካካሰውና እያዳከመው ነው። አቶ መለስ የገነቡት በግለሰብ ላይ የተመሰረተ አመራር፣ እርሳቸው ከቦታው ሲጠፉ፣ የእርሳቸውን ቦታ ተክቶ ትእዛዝና መመሪያ የሚሰጥ አካል እንደጠፋ አድርጎታል። የቀናት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በኢህአዴግ ውስጥ የተጀመረው ትርምስ ወደ አደባባይ መውጣቱ እንደማይቀር ነው ምንጫችን የገለጡት።

በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የአቶ መለስ የጤና ሁኔታ በይፋ እንደማይነገር፣ ነገር ግን የሰራዊቱ የአመራር አባላት ግራ መጋባት እንደሚታይባቸው ምንጫችን ገልጠዋል። ህወሀት መከላከያውና ቁልፍ የሚባሉትን ስልጣኖችን ይዞ ለመቆየት በአቶ ስብሀት ነጋ ፊታውራሪነት እንቅስቃሴ የጀመረ ቢሆንም፣ በብአዴንና በኦህዴድ በኩል እርምጃቸው አልተወደደላቸውም እንደምንጫችን ጥቆማ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አቶ መለስ አሁንም ማገገሚያ ቤት ውስጥ አለመውጣታቸውን የግንቦት7 ራዲዮ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል። ራዲዮኑ ትናንት ባሰራጨው ዘገባ ፣ አቶ መለስ ” ቤልጂዬም ብራስል በሚገኘው የሴይንት ሉክ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ ህይወታቸው አደጋ ላይ የወደቁ ሰዎች የመተንፈሻና የፈሳሽ ምግብ ቱቦዎ ተገጥሞላቸው በሚተኙበት የሪከቨሪ ሩም እየተባለ በሚጠራው የህክምና ክፍል ውስጥ ይገኛሉ ብሎአል።

ላለፉት 3 ሳምንታት እራሳቸውን መቆጣጠር በማይችሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ  ምንጮቹን ቅሶ ዘገበው ራዲዮው ፣ ከአሁን አሁን ይሞታሉ ተብሎ ሲጠበቅ ነፍሳቸው መለስ እንደሚልና ተሽሎዋቸዋል ተብሎ ሲታሰብ ደግሞ ወዲያውኑ ልቦናቸውን እንደሚስቱ ራዲዮው ገልጧል።

የግንቦት 7 መረጃና ክትትል ጓዶች ባካሄዱት ስውር ክትትል አምባሳደር ብርሃኔ ገብረክርስቶስ ዘወትር ጠዋት በአንድ አፍሪካዊ በሚሽከረከር የኮር ዲፕሎማቲክ መኪና መለስ ዜናዊ ብራሰልስ ውስጥ ወደተኛበት ሆስፒታል እንደሚመላለስ ለማረጋገጥ ተችሏል ብሎአል።

በአንጻሩ የመለስ ዜናዊ ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ አዜብ መስፍን የአምባሳደር ብርሃኔ ገብረክርስቶስን ግማሽ ያክል እንኳ ካባለቤታቸው ጋር ለመቆየት አለመፈለጋቸው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉትን ሁሉ ያስገረመ ሆኖአል ሲል ራዲዮው ዘግቧል።

የአቶ መለስ ወደ ስልጣን የመመለስ እድል ወደ ዜሮ እየተጠቃ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ አገሪቱ አንድነቷን ጠብቃ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ይመሰረት ዘንድ የተቃዋሚውና የመንግስት ባለስልጣናት ሚና ወሳኝ መሆኑን ወጣቱ የፖለቲካ ተንታኝ፣ ጸሀፊና የአርነት ትግራይ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ አስራት አብረሀ ለኢሳት ተናግረዋል ::

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide