የዚምባቡዌ ወታደራዊ አዛዦች ከሚኒስትሮችና ከሮበርት ሙጋቤ ጋር በድርድር ላይ ናቸው

(ኢሳት ዜና–ሕዳር7/2010)በዚምባቡዌ የሀገሪቱን ስልጣን የተቆጣጠሩት ወታደራዊ አዛዦች ከሚኒስትሮችና በቁም እስር ላይ ከሚገኙት ሮበርት ሙጋቤ ጋር በድርድር ላይ መሆናቸው ታወቀ።

ድርድሩን በዋናነት የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ ሳድክ እየመራው መሆኑ ታውቋል።

የአፍሪካ ሕብረት በበኩሉ የወታደራዊው ሃይል ስልጣኑን በሃይል መቆጣጠሩን እንደማይቀበለው አስታውቋል።

በዚምባቡዌ ወታደራዊ አዛዦች የሀገሪቱን መንበረ ስልጣን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ዛሬ ወታደራዊ አዛዦቹ ከሚኒስትሮች እንዲሁም በቁም እስር ላይ ከሚገኙትና ሀገሪቱን ለ37 አመታት ከመሩት ሮበርት ሙጋቤ ጋር በድርድር ላይ መሆናቸው ተነግሯል።

ቢቢሲ ከሐራሬ እንደዘገበው ድርድሩ እየተመራ ያለው ሳድክ በመባል በሚታወቀው የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ አማካኝነት ነው።

የዚምባቡዌ የተቃዋሚ መሪ የሆኑት ሞርጋን ቫንጊራይ ሙጋቤ ስልጣኝቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንዲለቁ ጠይቀዋል ተብሏል።

ቢቢሲ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው የ93 አመቱ ሮበርት ሙጋቤ ሕጋዊ ፕሬዝዳንት ነኝ በማለት ስልጣናቸውን ላለመልቀቅ እያንገራገሩ መሆኑ ተሰምቷል።

የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የጊኒው አልፋ ኮንዴ ሕብረቱ የወታደራዊው ሃይል ስልጣኑን በሃይል መቆጣጠሩን አይቀበለውም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ኮንዴ ወታደራዊ ሃይሉ ወደ መጣበት ጦር ሰፈር እንዲመለስና ሕገ መንግስቱ እንዲከበርም ጠይቀዋል።

ዚምባቡዌ ከነጮች አገዛዝ ነጻ ከወጣችበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1980 ጀምሮ በስልጣን ላይ የቆዩት የ93 አመቱን ሙጋቤን ማን ይተካው የሚለው ውዝግብ በመሪው ፓርቲ ዛኑ ፒ ኤፍ ውስጥ ክፍፍልን ፈጥሯል።

ሙጋቤና ተከታዮቻቸው ስልጣኑን የ52 አመቷ ግሬስ ሙጋቤ እንዲረከቡ ይፈልጋሉ።

ላለፉት 21 አመታት በትዳር ከሮበርት ሙጋቤ ጋር የቆዩት ግሬስ ሙጋቤ ከሳምንት በፊት ምክትል ፕሬዝዳንቱን ኤመርሰን ናንጋጋዋን ከስልጣን በማስወገድ ረገድ ሚና እንደነበራቸው ታውቋል።

በዛኑ ፒ ኤፍ ውስጥ የሙጋቤና የባለቤታቸው ተቀናቃኞች ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ናንጋጋዋ ስልጣኑን እንዲረከቡ ይፈልጋሉ።

የምክትል ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ ነበር ወታደራዊ ባለስልጣናት ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ውስጥ ያለውን የስልጣን ሽኩቻ እናስቆማለን በሚል ጣልቃ የገቡት።

ወታደራዊ ባለስልጣናቱ የምክትል ፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች እንደሆኑም ይነገራል።

ከዚህ በተጨማሪም ወታደራዊው ክፍል ግሬስ ሙጋቤና ተከታዮቻቸው ስልጣኑን ለመቆጣጠር እያደረጉ ያለውን ጥረት ለማስቆም እየሰሩ እንደሆነም እየተነገረ ነው።

ለረጅም አመታት ሙጋቤን የሚያውቋቸው የሮማ ካቶሊክ ቄስ የሆኑት ፊደሊስ ሙኮኖሪ በመኖሪያ ቤታቸው በቁም እስር ላይ ያሉት ሙጋቤ ወደፊት ከወታደራዊ ሃይሉ ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ድርድር ላይ መሆናቸውም ተሰምቷል።