የኮልፌ ቀራኒዮ ነዋሪዎች ጥያቄያቸውን እንዳያቀርቡ ታገዱ

ሰኔ ፲፪( አሥራ ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ በኮልፈ ቀራኒዮ ክ/ከተማ ወረዳ 3 ካራ ቆሬ/ ሬጲ አካባቢ ሰኔ 03 ቀን 2009 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ በከፍተኛ ቃጠሎ የጋየውን የሮያል ስፖንጅ ፋብሪካ ተከትሎ እሁድ ሰኔ 4/09 ከ 1200 በላይ ነዋሪዎችን የሚወክሉ 205 የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ለ3 ሠዓታት ያክል ተሰብስበው ፋብሪካው በህብረተሰቡ ላይ ያደረሰውን ጉዳት በዝርዝር በመጻፍ ለመስተዳድር ባለስልጣናት ለማቅረብ ወስነው ነበር። ነዋሪዎቹ በልጆቻቸውና በእንስሳት ጤናና አእምሮ ላይ ያመጣውን ጉዳት በመዘርዘር ፋብሪካው ከመኖሪያ አካባቢው እንዲነሳ እንዲሁም ዘላቂ መፍትሄ እስኪሰጠው ድረስ ‹‹ ሥራ እንዳይጀምር…›› እንዲደረግና በ3 ቀናት ውስጥ ምላሽ የሮያል ስፖንጅ ፋብሪካ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ፣ 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ አዋቅረዋል።
የወረዳው መስተዳድር ለህዝቡ ጥያቄ መልስ በመስጠት ፋንታ፣ ለኮሚቴው ‹‹ ህዝቡ እንዳይሰበሰብ ›› ከባድ ማስጠንቀቂያ ማስተላለፉን፣ የኮሚቴው አባላት በየቤቱ እየዞሩ ለነዋሪዎች ይህንኑ እንዲገልጹ ማዘዛቸውን፣ የኮሚቴው አባላት ሰኔ 10/2009 ዓም ምሽት ላይ ቤት ለቤት እየዞሩ ለነዋሪዎች ተናግረዋል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት እገዳው የተጣለው አንድም የፋብሪካው ባለቤት ጉዳዩን ለማዳፈን ጥረት በማድረጉ ፣ ወይም ተቃውሞው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያድጋል ከሚል ፍርሃት ሊሆን ይችላል።
ህዝቡ ‹‹ መንግስት የለም ፣ ከአካባቢው ከ500 ቤተሰብ ወይም ከ 3ሺህ ነዋሪዎች በላይ ወገናዊነቱ ለአንድ ባለሃብት ›› ሆኗል በማለት እያማረሩ ነው።