የኢትዮጵያ የመከራ ዘመን እንዲያበቃ፣ፍቅርና አንድነት እንዲታወጅ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 1/2010)የኢትዮጵያ የመከራ ዘመን እንዲያበቃ፣ፍቅርና አንድነት እንዲታወጅ በውጭ የሚኖሩ አባቶች ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያን አዲስ አመት 2010 በማስመልከት በሐገር ቤትና ከሐገር ውጭ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ሰባኪያን የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ እንዲሁም የፈርስት ሒጅራ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ሐጂ ነጂብ መሀመድና የፈርስት ሒጅራ ፋውንዴሽን ኢማም ሼህ ካሊድ ኡመር ፣የአዲስ ኪዳን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ፓስተር ሙሉጌታ አባተና ከኤልሻዳይ አገልግሎት ፓስተር ተፈራ ፈቃደ በኢሳት በኩል ባስተላለፉት መልእክት ፍትህና ነጻነት፣ፍቅርና ሰላም እንዲታወጅ ጥሪ አቅርበዋል።

ብጹእ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዮስ አዲሱን አመት 2010ን በማስመልከት ባስተላለፉት በዚህ መልእክት እግዚአብሔር ለሕዝብ የሚራራ መሪ እንዲያስነሳ ተግቶ መጸለይና መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን በመላው አለም ተበትነው በውርደት ጭምር የሚኖሩበት፣በሀገር ቤትም ብዙዎች በእስራትና ሰብአዊ መብታቸው ተገፎ በሞት ጥላ ስር የሚኖሩበት ሁኔታ እንዲያበቃ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ምእመናን ተግተው እንዲጸልዩ ያሳሰቡት ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዮስ አመቱ የምህረት አመት እንዲሆን ለታሰሩት መፈታት፣ለተጠቁት ነጻነት ሊታወጅላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣መብትና ነጻነት ተግተን እንጸልይ ሲሉ መንፈሳዊ ጥሪያቸውን ያስተላልፉት ብጹእ ወቅዱስ ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዮስ እግዚአብሔር እድሜና ዘመንን የሰጠን እንድንጠፋበት ሳይሆን እንድንተባበር፣እንድናንስ ሳይሆን እንድናድግበት ነው በማለት የፍቅርና የአንድነት ጥሪ አድርገዋል።

የፈርስት ሒጅራ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ሐጂ ነጂብ መሀመድ አዲሱን አመት በማስመልከት ባስተላለፉት መልእክት አዲሱ አመት በብሔር ሳንከፋፈል በኢትዮጵያዊነት ስሜት በጋራ እናክብረው በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

አመቱ ኢትዮጵያውያን ከችግር የሚወጡበትና ፍትህ የሚያገኙበት እንዲሆን ተመኝተዋል።

የፈርስት ሒጅራ ፋውንዴሽን ኢማም ሼህ ካሊድ ኡመር በበኩላቸው ለኢትዮጵያውያን ሁሉ መልካሙን ተመኝተዋል።

ፍትህና ሰላም የበላይ የሚሆኑበት ዘመን እንዲሆንም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የአዲስ ኪዳን የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ፓስተር ሙሉጌታ አባተ ዘመኑ የፍትህ፣የእኩልነትና የሰላም እንዲሆን ምኞታቸውን ሲገልጹ ፓስተር ተፈራ ፈቃደ ከኤልሻዳይ አገልግሎት ደግሞ ዘመኑ እስረኞች የሚፈቱበት፣የእኩልነትና የፍትህ ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል።