የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አቅጣጫ ቀይሮ ካናዳ ሀሊፋክስ ስታንፊልድ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ተገደደ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 2/2010) ከአዲስ አበባ ከተማ ተነስቶ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ይበር የነበረ ቦይንግ 777 የበረራ ቁጥር 500 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አቅጣጫ ቀይሮ ካናዳ ሀሊፋክስ ስታንፊልድ አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ተገደደ።

የአየር መንገዱ ምንጮች እንደገለጹት ዋሽንግተን ዲሲ ጥቅምት 1/2010 ከጠዋቱ 2 ሰአት ከ40 ደቂቃ መድረስ የነበረበት አውሮፕላን እስከ ከሰአት 7 ሰአት ከ22 ድረስ መዘግየቱም ታውቋል።

ማክሰኞ ምሽት ከአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሳው የበረራ ቁጥር 500 የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 777 አውሮፕላን ደብሊን አየርላንድ ነዳጅ ለመሙላት ያደረገው ጉዞ በተያዘው ፕሮግራም መሰረት የተካሄደ ነበር።

ነገር ግን ከደብሊን ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ሲጓዝ አንድ መንገደኛ አውሮፕላኑ ወስጥ ሕይወታቸው በማለፉ ካናዳ ሀሊፋክስ ስታንፊልድ አውሮፕላን ማረፊያ በካናዳ ሰአት አቆጣጠር ከጠዋቱ 3 ሰአት ከ55 ደቂቃ አርፏል።

እስከ ቀትር 6 ሰአት ከ15 በዚያው አውሮፕላን ማረፊያ ቆይታ አድርጎ ከ1 ሰአት 5 ደቂቃ በረራ በኋላ ወደ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ መድረሱ ታውቋል።

የበረራ ቁጥር 500 የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መስመሩን ለመቀየር ምክንያት የሆነውና ካናዳ ለማረፍ የተገደደው አንዲት ናይጄሪያዊት ተሳፋሪ በመታመማቸውና በኋላም ህይወታቸው በማለፉ እንደሆነ ታውቋል።