የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የመንግስት ቃል አቀባይን ተቹ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 15/2010)የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የመንግስት ቃል አቀባዩን ተቹ::

ቃል አቀባዩ ነገሬ ሌንጮ በተሳሳተ መልኩ መረጃ ያቀረቡ የመገናኛ ብዙሃንን ላይ ህግን መሰረት በማድረግ እርምጃ ይወሰዳል በማለት የሰጡትንም መግለጫ የግላቸውን እንጂ የመንግስት አቋም አይደለም ሲሉ አጣጥለውታል።

ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዘርአይ ጨምረውም በብሮድካስት ሚዲያው ላይ የሚታይ አደገኛ አዝማማሚያ መኖሩንም ጠቁመዋል።

የህወሃት ነባር ታጋይና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዘርአይ አስገዶም በብሮድካስት ሚዲያው ላይ የሚታይ አደገኛ አዝማማሚያ መኖሩን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።

እንደ እሳቸው አባባል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ያሉትን ግጭቶች የመገናኛ ብዙሃኑ የሚዘግቡበት መንገድ ትክክል ያልሆኑና የበለጠ ግጭትን የሚፈጥሩ ናቸው።

የመገናኛ ብዙሃኑ ጠንካራ አለመሆናቸውና አዘጋገባቸውም የተሳሳተ መሆኑ ለማህበራዊ ሚዲያው እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል ሲሉም ያክላሉ።

አሁን ላይ ከግሉም ሆነ ከሕዝብ መገናኛ ብዙሃን የሚታዩ ያሉ አደገኛ አዝማሚያዎች መኖራቸውንም በግልጽ አስቀምጠዋል።

ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ ህግን መሰረት በማድረግ እርምጃ ይወሰዳል በማለት የሰጡትንም መግለጫ የግላቸውን እንጂ የመንግስት አቋም አይደለም ሲሉ አቶ ዘርአይ አጣጥለውታል።

የሰጡት መግለጫም የግል አስተያየታቸው እንጂ የመንግስት አቋም እንዳልሆነ አረጋግጠዋል።

አቶ ዘርአይ እንደሚሉት ከሆነ የሚዲያ ተቋማት ላይ ርምጃ መውሰድ የሚችለው የብሮድካስት ባለስልጣንና ፍርድ ቤት እንጂ የመንግስት ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት እንዳልሆነም ተናግረዋል።

በሕወሃት ባለስልጣናት ዘንድ አንዱ የተናገረውን አንዱ የመሻርና የማጥላላት ሂደት ከበፊቱ በበለጠ መልኩ እይተባባሰ መምጣቱን በተለያየ ጊዜ የሚገልጹት ታዛቢዎች የአሁኑ የአቶ ዘርአይ አስገዶም አስተያየትም የዚሁ ነጸብራቅ ነው ብለዋል።