የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ መንግስት በተቃዋሚና ሃሳባቸውን በነጻነት በሚገልጹ ዜጎች ላይ የሚወስደውን ፖለቲካዊ ማዋከብ በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳሰቡ

ኢሳት (ግንቦት 11 ፥ 2009)

ከአስር የሚበልጡ የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያ መንግስት በተቃዋሚና ሃሳባቸውን በነጻነት በሚገልጹ ዜጎች ላይ የሚወስደውን ፖለቲካዊ ማዋከብ በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳሰቡ።

የምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት አጋር ብትሆንም፣ ሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስትፈጽም ዝም ብለውን እናያለን ማለት አይደለም ማለታቸውን አፍሪካ ኒውስ የምክር ቤት አባላቱ በጋር ያወጡትን መግለጫ ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

የሜሪላንድ እና የፍሎሪዳ ግዛት ተወካይ የሆኑት ቤን ካርዲን እና ማርኮ ሩቢዮ በ14 ሴናተሮች የቀረበውን ሃሳብ ማስተባበራቸው ታውቋል።

በአስቸኳይ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አሳሰቧቸው እንደሚገኝ የገለጹት የምክር ቤት አባላቱ በቅርቡ በሃገሪቱ ተካሄዶ ከነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ጉዳይ በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት አሳስበዋል።

“በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታና የፖለቲካ አባላት እስራት ስጋትን አሳድሮብናል” ሲሉ የሜሪላንድ ግዛት ሴናተሩ ካርዲን ገልጸዋል።

የፍሎሪዳ ግዛት ተወካዩ ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው የሜሪካ መንግስት የሰብዓዊ መብት ሁኔታውን ማሻሻል ባልቻለው የኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚሰማውን ስጋት ከመግለፅ መቆጠብ እንደሌለበት አሳሰበዋል።

ከሌሎች ባልደርቦቻቸው ጋር በመሆኑንም መንግስት የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብርና በፖለቲካ አካላት ላይ የሚወስደውን ማዋከብ እንዲያቆም የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥለው ሴናተሩ አክለው ገልጸዋል።

የ14 ግዛቶች ሴናተሮች በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝና በተለያዩ አካላት የሚፈጽመው ማዋከብና እንግልት ስጋትን አሳድሮባቸው እንደሚገኝ በአጽንዖት አብራርተዋል።

ባለፈው አመት ሁለት ታዋቂ የምክር ቤት አባላት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችንና የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት በማስተባበር የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ እርምጃውን እንዲወስድ የውሳኔ ሃሳብ ለማቅረብ ዘመቻ መክፈታቸው ይታወሳል።

ይኸው የውሳኔ ሃሳብ በበርካታ አባላት ዘንድ ድጋፍ እያገኘ መምጣቱን አስተባባሪዎቹ በቅርቡ መገልጻቸው አይዘነጋም።