የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የኦሮሞ ተወላጆች ከክልሉ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጡ

(ኢሳት ዜና –መስከረም 2/2010)የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የኦሮሞ ተወላጆች ከክልሉ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠታቸው ታወቀ። ይህን ተከትሎም በመቶዎች የሚቆጠሩት ወደ ሀረር ከተማ መሸሻቸው ተገልጿል።

በምስራቅ ኢትዮጵያ በሶማሌና ኦሮሚያ ወሰኖች ላይ የተጀመረው ግጭትም መባባሱ ተሰምቷል።
በምስራቅ ሀረርጌ በርካታ ከተሞች ተቃውሞ ተቀስቅሷል። በደደርና አወዳይ በትንሹ 3 ሰዎች ተገድለዋል።

በኦሮሞና ሶማሌ ክልል ወሰኖች ዙሪያ የተጀመረው ውጊያ በቀጠለበት ከሶማሌ ክልል የኦሮሚያ ተወላጆች እንዲወጡ መደረጋቸው በኦሮሚያ የተነሳውን የህዝብ ጥያቄና የፖለቲካውን አቅጣጫ ትኩረት ለማስቀየስ እንደሆነ እየተነገረ ነው።

ለኢሳት በደረሰው መረጃ በሶማሌ ክልሉ ፕሬዚዳንት አብዲ ትዕዛዝ የኦሮሞ ተወላጆች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ሃረር ምስራቅ እዝ ጽ/ቤት እንዲሰፍሩ ተደርጓል። ይህ ዘገባ እስኪጠናቀር ድርስ ባለው መረጃ በርካታ ነዋሪዎች ከሶማሌ ክልል ሸሽተው ወደ ሀረር ከተማ ገብተዋል።

የምስራቅ እዝ የጦር አባላት ህዝባዊ አመጽ ወደተነሳባቸው ከተሞች እየተንቀሳቀሱ ነው።
በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት ያስታጠቀው የሶማሌ ልዩ ሃይል በከባድ መሳሪያዎች ታጅቦ ወደ ተለያዩ የኦሮሚያ አዋሳኝ ከተሞች መግባቱ ታውቋል።

በአወዳይና በደደር የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል። ሁለት ሰዎች መሞታቸው እየተነገረ ነው። አካባቢው ወደለየለት የዕልቂት ቀጠና እንዳያመራ ስጋቶች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ነው።
ኢሳት ያነጋገራቸው የመኢሶ ነዋሪ እንደሚሉት ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የሶማሌ ልዩ ሃይል የኦሮሞ ተወላጆችን ለማጥቃት ተሰማርቷል።

በመጪው ቀናት በአካባቢው የሚፈጠረው ግጭት አሳሳቢ እንደሆነም ነዋሪዎች በስጋት በመግለጽ ላይ ናቸው።

በምስራቅ ሀረርጌ ተቃውሞው ተስፋፍቷል። በአወዳይ፣ ደደር፣ ቆቦ እና ጭናክሰን ከተሞች ከፍተኛ ተቃውሞ እየተካሄደ ነው።

ወደ አዲስ አበባ፣ ጅጅጋ እና አጎራባች ከተሞች የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ስራ አቁመዋል። በአወዳይ እስካሁን የመከላከያ ጂፕን ጨምሮ 4 ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል።

ወደ ሶማሌ ክልል የሚያመሩ ጫት የጫኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት የተሰነዘረ ሲሆን በሶስቱ ላይ በተወሰደ እርምጃ ከጫኑት ጫት ጋር ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ መደረጋቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በደደርና በአወዳይ የተደረጉት ሰልፎች የሰው ህይወት የጠፋባቸው ሲሆን ደደር ላይ 3 ሰዎች በፖሊሶች ቆሰለዋል።

አወዳይ ላይ እስካሁን ባለው መረጃ 2 ሰዎች እንደሞቱና በርካታ ሰዎች እንደቆሰሉ ታውቋል። ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ እንደሚሉት የሶማሌ ልዩ ሃይል የወረዳ የፓርቲ አመራሮች ላይ ያተኮረ ጥቃት በመሰንዘር ላይ ናቸው።

ህዝቡ ራሱን ለመከላከል ተዘጋጅቷል ያሉት ነዋሪው ከዚህ ጥቃት ጀርባ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እጅ አለበት።

ዘግይተው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ሁኔታዎች በጣም አሳሳቢ ሆነዋል። የህወሃት መንግስት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን በማመን ቁጥሩን ለመግለጽ ለጊዜው አስፈላጊ አይደለም የሚል ምላሽ ሰጥቷል።