የሶማሊያ መንግስት ኦብነግን በአሸባሪነት መፈረጁን ግንባሩ ህገወጥ ፍረጃ ሲል አጣጣለው

(ኢሳት ዜና–ጳጉሜ 2/2009) የሶማሊያ መንግስት ኦብነግን በአሸባሪነት መፈረጁን የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ህገወጥ ፍረጃ ሲል አጣጣለው።

የሶማሊያ ፓርላማን ስልጣን በመጋፋት በፕሬዝዳንት ፋርማጆ የሚመራው የሚኒስትሮች ምክርቤት ውሳኔውን ማሳለፉ የሀገሪቱን ህገመንግስት የጣሰ ነው ሲልም ኦብነግ አስታውቋል።

በቅርቡ ለህወሀት መንግስት ተላልፈው በተሰጡት የኦብነግ አመራር አባል አብዲካሪን ሼህ ሙሴ ምክንያት በሶማሊያ ከፍተኛ ቁጣ የተቀሰቀሰ ሲሆን ትላንት የፕሬዝዳንት ፋርማጆ መንግስት ኦብነግን በአሸባሪነት መፈረጁ የተቀሰቀሰውን የህዝብ ቁጣ ያባብሰዋል ተብሎ ተሰግቷል።

የኦብነጉ ከፍተኛ አመራር አብዲካሪን ሼህ ሙሴ ጉዳይ ለሶማሊያ ሌላ የውዝግብ ግንባር ከፍቶባታል።
ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ መንግስት ተላልፈው የተሰጡት የአብዲካሪን ሼህ ሙሴ ጉዳይ በሶማሊያ በመንግስትና በህዝቡ መካከል የከረረ ፍጥጫን ፈጥሯል።

ቀድሞውኑ የህዝብን ድምጽ አግኝተው ለቤተመንግስት የበቁበት ዋነኛ ጉዳይ ለህወሀት መንግስት ፊት በማይሰጡበት አቋማቸው እንደሆነ የሚነገርላቸው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሀመድ ፋርማጆ አሁን ላይ ከህወሀት ጋር አንድ መስመር ላይ ያቆማቸው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኗል።

የህዝቡ ተቃውሞ በተጋጋለበት፣ በመንግስታቸው ውስጥም ህግ አውጪዎችና ታላላቅ ሰዎች ስልጣን እንዲለቁ እየጠየቁ ባልበት በዚህን ሰሞን ፕሬዝዳንት ፋርማጆ በእሳት ላይ ቤንዚን የሚጨምር አቋም መያዛቸው ትላንት ተሰምቷል።

ስልጣን ያለው የሶማሊያ ፓርላማ ባልወሰነበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግን በአሸባሪነት መፈረጁ ፍጥጫውን አባብሶታል።
የፕሬዝዳንት ፋርማጆ አመራር የኦብነጉን አመራር ለህወሀት መንግስት አሳልፈው መስጠታቸውንም ተገቢና ለደህንነት ሲባል የተወሰደ ህጋዊ እርምጃ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው።

የፕሬዝዳንት ፋርማጆ ቃል አቀባይ አብዱራሂም ኦማር ኦስማን ትላንት በሞቃዲሾ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ በሁለቱ መንግስታት መካከል በተደረገ ስምምነት መሰረት የአሸባሪ ቡድን መሪ የሆኑት ሼህ ሙሴ ተላልፈው ተሰጥተዋል ብለዋል።
በዚህም የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግን መንግስታቸው አሸባሪ ብሎ እንደፈረጀው ማረጋገጫ ሰጥተዋል ተብሏል።

ኦብነግ የሶማሊያ መንግስትን ውሳኔ የሀገሪቱን ህግ የጣሰና የፓርላማውን ስልጣን የተጋፋ እርምጃ ነው ሲል አውግዞታል።

አቶ ሀሰን አብዱላሂ የኦብነግ ቃል አቀባይ እንደሚሉት ፋርማጆ ለስልጣን የበቁበትን አቋማቸውን በመካድ የህወሀት መንግስትን ፍረጃ ያስተጋቡበት እርምጃ ነው።

የፕሬዝዳንት ፋርማጆ መከላከያና ፍረጃ በሶማሊያውያን ዘንድ ሌላ ቁጣ ቀስቅሷል።
የፓርላማ አንዳንድ አባላት ጥያቄ ከማንሳት ጀምሮ በኦብነግ ላይ የተላለፈው የአሸባሪነት ፍረጃ ህግን የተከተለ አይደለም በሚል እንዲመረመር ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው።

በህወሀትና በሶማሊያ መንግስታት መሀል የተደረገው የ2015ቱ ስምምነት በክልሎች መሀል የተከናወኑ እንጂ በሀገር ደረጃ የተካሄደ እንዳልሆነ ኢሳት ከደረሰው የስምምነቱ ሰነድ ማረጋገጥ ተችሏል።
በሶማሊያው ጋልሙዲግ ግዛትና በኢትዮጵያው የሶማሌ ክልል መሪዎች መካከል የተደረገው ስምምነትን በመጥቀስ የሶማሊያ መንግስት ሼህ ሙሴን አሳልፎ ለሰጠበት እርምጃው እንደ ማስረጃ ማቅረቡ እያነጋገረ ነው።

የጋልሙዲግ ግዛት የቀድሞ አስተዳዳሪ አብዱልከሪም ጉሌድ ለአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ የሶማሊኛ ፕሮግራም በሰጡት ቃለመጠይቅ ፋርማጆ በክልሎች ደረጃ የተደረገውን ስምምነት መጠቀማቸው ትልቅ ስህተት ነው ብለዋል።

ሌሎች የሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናትን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መሃል እንዳልተፈጸመ ይገልጻሉ።
ፋርማጆ ወደስልጣን የመጡበት ዋናው አቋማቸው ዛሬ አብሯቸው የለም። ከህወሀት መንግስት ጋር ለጊዜው መስመራቸው ተገናኝቷል።

በሀገራቸው የሚገኘውን በህወሀት የሚመራውን ጦር እንዲያስለቅቁ በህዝባቸው የሚጠየቁት ፋርማጆ የተነሳባቸውን ተቃውሞ ወደጎን ችላ ብለው በኦብነግና በአመራር አባሉ ላይ በወሰዱት እርምጃ ጸንተዋል።

ይህም ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው። ከወዲሁ ተቃውሞ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የሶማሊያ ፓርላማም በጉዳዩ ላይ ይነጋግርበታል ተብሎ ይጠበቃል። በ2011 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ህወሀት በተቆጣጠረው ፓርላማ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ የነጻነትና የፍትህ ታጋይ ግንባር እንጂ አሸባሪ አይደለሁም ብሏል።