የሜክሲኮ ደቡባዊ የባህር ዳርቻ በርእደ መሬት ተመታ

(ኢሳት ዜና –ጳጉሜ 3/2009) የሜክሲኮ ደቡባዊ የባህር ዳርቻ በሪክተር ስኬል 8 ነጥብ 2 በተመዘገበ ርእደ መሬት ተመታች።

በሀገሪቱ የመቶ አመት ታሪክ ውስጥ በከባድነት በተመዘገበው በዚህ ርእደ መሬት እስካሁን 33 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።

በሌላ በኩል የአሜሪካ የአደጋ ጊዜ ኤጀንሲ ሃሪኬን ኢርማ ፍሎሪዳን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጉረቤት አካባቢዎችንም ሊያጠፋ ይችላል ሲል ማስጠንቀቂያውን ሰጥቷል።

የሜክሲኮን ደቡባዊ የባህር ዳርቻን የመታው ርእደ መሬት በመቶ አመት የሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ከባዱ ነው ሲሉ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኤኔሪኬ ፔናኔቶ ገልጸውታል።በሪክተር ስኬል 8 ነጥብ 2 በተመዘገበው ርእደ መሬት እስካሁን 33 ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የሟቾቹ ቁጥር ከዚህ በላይም ሊጨምር እንደሚችልም ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።

በርእደ መሬቱ ኦክሳካና ቺአፓስ ግዛቶች በከባዱ መጎዳታቸው ታውቋል።እነዚህ ግዛቶች ደግሞ 9 ሚሊየን ያህል ሰዎች መኖሪያ ናቸው።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1985 የሜክሲኮ ከተማን የመታው ርእደ መሬት በሺ ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን ዘገባው አስታውሷል።

እንደ ሲኤን ኤን መረጃ ከሆነ ደግሞ የሜክሲኮ የባህር ዳርቻን ጨምሮ፣ጓቲማላ፣ፓናማ፣ኤልሳልቫዶር፣ኮስታሪካ፣ኒካራጉዋ፣ሁንዱራስና ኢኳዶር በሱናሚ አውሎ ንፋስ ሊመቱ ይችላሉ።

በሌላ በኩል የአሜሪካ የአደጋ ጊዜ ኤጀንሲ ሃሪኬን ኢርማ ፍሎሪዳን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጉረቤት አካባቢዎችንም ሊያጠፋ ይችላል ሲል ማስጠንቀቂያውን ሰጥቷል።
ደቡባዊ ፍሎሪዳን ያመታል በተባለው አውሎ ንፋስ ምናልባትም አካባቢው ለቀናት ከኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት ውጪ ሊሆን ይችላል ከ100 ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ መጠለያ ሊያስፈልጋቸው ይችላል ሲል ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል።

በካሪቢያን አካባቢ ኢርማ አውሎ ንፋስ ባደረሰው ጉዳይ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ያህል ሰዎች ተጠቂ ሆነዋል።
የአካባቢው ባለስልጣናት አሁንም አውሎ ንፋሱ ከዚህ በላይ አደጋ ሊያስከትል ይችላልና በሁሉም አካባቢዎች ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲሉ በመወትወት ላይ ናቸው።

ሚያሚ ከኣአውሎ ንፋሱ ጋር በተያያዘ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ አለም አቀፍ በረራዎችን መሰረዟ ተሰምቷል።

እስከ ቀጣዩ ሰኞም አብዛኞቹ አየር መንገዶች በረራዎቻቸውን ሊሰርዙ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአሜሪካ የአየር ትንበያ መስሪያ ቤት ደግሞ በቀጣዮ ቅዳሜና እሁድ ኢርማ አውሎ ንፋስ በሰአት 165 ማይል የሚጓዝ ንፋስ ሊያስከትል ይችላል ሲል ከወዲሁ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ላይ ነው።

በቀጣዩ እሁድ አውሎ ንፋሱ ደቡባዊ ፍሎሪዳን ይመታል መባሉን ተከትሎም 500 ሺ ያህል ሰዎች አካባቢያቸውን እንዲለቁ ተነግሯቸዋል።

ኢርማ አውሎ ንፋስ ደቡባዊ ፍሎሪዳን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ የደቡብ ምስራቅ የአሜሪካ ግዛቶችንም ሊጎበኝ ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግ ባለሙያዎች በመናገር ላይ ናቸው።

ኢርማን ተከትሎ የካሪቢያን ደሴቶችን ይመታል ተብሎ የሚጠበቀው ጆስ አውሎ ንፋስ ደግሞ ሌላኛው ስጋት ሆኗል።