ከኢርማ አውሎ ንፋስ ጋር በተያያዘ 10 ሰዎች ሞቱ

(ኢሳት ዜና–ጳጉሜ 2/2009) የሰሜን ካሪቢያ ደሴቶችን እየመታ ባለው ኢርማ አውሎ ንፋስ እስካሁን 10 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

በአደግኝነቱ በ5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢርማ አውሎ ንፋስ የደሴቲቱን አብዛኛውን ክፍል ከጥቅም ውጪ ማድረጉን መረጃዎች አመልክተዋል።

አውሎንፋሱ እሁድ ወደ ደቡባዊ ፍሎሪዳ ይሻገራል መባሉን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት ነግሷል።

ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ተነስቶ የሰሜን ካሪቢያን ደሴቶችን እየመታ ያለው ኢርማ አውሎ ንፋስ እስካሁን የ10 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።–በርካቶችን መኖሪያ አልባ አድርጓል።

በአደግኝነቱ በ5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢርማ አውሎ ንፋስ 95 በመቶ የሚሆነውን የደሴቲቱን አካባቢ ምድረ በዳ አድርጓል።የአንቲጉዋና የባርቡዳ ደሴቶች ደግሞ በአውሎ ንፋሱ በከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ናቸው።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ 50 በመቶ የሚሆኑት የባርቡዳ ደሴት ነዋሪዎች መጠለያ አልባ ሆነዋል።አውሎ ንፋሱ የብሪቲሽ ቨርጂን ደሴትንም ከጥቅም ውጪ አድርጎት ማለፉ ተሰምቷል።

በሰአት 180 ማይልስ የሚጓዘውና ፖርቶሪኮን የመታው ኢርማ አውሎ ንፋስ 1 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎችን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጭ አድርጓቸዋል።

ኢርማ አውሎ ንፋስ ሀሙስ ማለዳ በሰሜናዊ ዳርቻ ወደ ዶሚኒካን ሪፐብሊክና ሀይቲ ተሻግሯል። ከሚጥለው ዝናብ ጋርም በተያያዘ አካባቢዎቹ 15 ኢንች በሚለካ ጎርፍ ሊጥለቀለቁ እንደሚችሉ መረጃዎች አመልክተዋል።

በሜክሲኮ የባህር ዳርቻና በካሪቢያን አካባቢ እየጣለ ያለው ዝናብ 20 ኢንች በሚለካ ውሃ አካባቢውን ሊያጥለቀልቅ ይችላል ሲሉ የአየር ትንበያ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በሴንት ሜሪ የሚሰማውን የኢራም አውሎ ንፋስን ድምጽ የጀት ሞተርን የሚመስል እጅግ አስደንጋጭ ድምጽ ሲል ሲ ኤን ኤን በዘገባው ገልጾታል።

75 ሺ የሚሆኑ ዜጎች ይኖሩበታል የሚባለው የካሪቢያን ደሴት በኢርማ አውሎ ንፋስ ከጥቅም ውጪ ሆኗል።

ተርክስና ካይኮስ ደሴቶች እንዲሁም ባሃማስ የበርካቶችን ህይወት ሊቀጥፍ ይችላል በተባለው ኢርማ አውሎ ቀጣይ ሰለባዎች ይሆናሉ ብሏል ዘገባው።

አውሎ ንፋሱ እሁድ ወደ ፍሎሪዳ ደቡባዊ ክፍል ይሻገራል መባሉን ተከትሎም በአካባቢው ውጥረት ነግሷል።

የፍሎሪዳ ሀገረ ገዢ ሪክ ስኮት አንድም ሳይቀር ሁሉም የግዛቲቱ ነዋሪ ለሕይወት አደጋ ነው ከሚባለው ከዚህ አውሎ ንፋስ ራሱን ለመታደግ መዘጋጀት አለበት ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የፍሎሪዳ አስተዳደር ከአደጋው ዜጎቹን ለመታደግ 7 ሺ የሚሆኑ ብሔራዊ ዘቦችን አዘጋጅቷል።