ታዋቂው ገጣሚና ጋዜጠኛ ሰለሞን ደሬሳ ከዚህ አለም በሞት ተለየ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 24/2010)ታዋቂው ገጣሚና ጋዜጠኛ እንዲሁም የፍልስፍና መምህር ሰለሞን ደሬሳ ከዚህ አለም በሞት ተለየ።

ሰለሞን ደሬሳ ከዚህ አለም በ80 አመቱ በሞት የተለየው በስደት በሚኖርባት አሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት ሚኒያፖሊስ ከተማ ነው።

ልጅነት፣ዘበት እልፊቱ ወለሎታትና የናይጄሪያው ጸሃፊ ወሌ ሾዬንካ ስብስብ ስራዎችን ጨምሮ 3 መጽሀፍትን ለአንባቢያን ያበረከተው ሰለሞን ደሬሳ የአንድ ልጅ አባት ነበር።

ገጣሚና ጋዜጠኛ እንዲሁም የፍልስፍና መምህር የነበረው ሰለሞን ደሬሳ የተወለደው በ1930 በምዕራብ ወለጋ ግምቢ አቅራቢያ ጩታ በተባለች መንደር መሆኑን የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል።

በ80 አመቱ ከዚህ ኣአለም በሞት የተለየው ሰለሞን ደሬሳ ልጅነት፣ዘበት እልፊቱ ወለሎታት የተባሉ ሁለት የግጥም ስራዎቹን አበርክቷል።

በተለይ ልጅነት የተሰኘችው የግጥም መድብሉ ከይዘት ይልቅ ቅርጽን የመረጠበት እንደነበር ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ሰለሞን ደሬሳ በፍልስፍና ትምህርቱና አስተምህሮቱም ይታወቅ ነበር።

ሰለሞን ደሬሳ በኢትዮጵያ ሬዲዮ በእንግሊዝኛ ዜና አንባቢነት ከተቀጠረበት ጊዜ አንስቶ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በሚታተሙ መጽሔቶችም በርካታ ጽሁፎችን አበርክቷል።

በኢትዮጵያ ሬዲዮ እስከ ምክትል ዋና ስራአስኪያጅነት ደረጃም ደርሶ ነበር።

በ1965 ለትምህርት ወደ ፈረንሳይ ያቀናው ሰለሞን በ1980 ወደ አሜሪካ በማምራትም ፍልስፍናና በሀይማኖት ንጽጽር ዲግሪውን ከያዘ በኋላ በሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ ሲያስተምር ቆይቷል።

ስለሰለሞን ደሬሳ የግጥም ችሎታ በሕይወት በነበረ ጊዜ ምስክርነቱን የሰጠው ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ሰለሞን ማለት ድንቅ ችሎታ ያለውና የግጥም ጥበብን የተካነ ባለሙያ ሲል ገልጾታል።

በሕመም ምክንያት ማስተማሩን ያቆመው ሰለሞን ደሬሳ ከረጅም ጊዜ ህመም በኋላ በተወለደ በ80 አመቱ ትላንት በሚኒሶታ ከተማ ማረፉን ቤተሰቦቹ ገልጸዋል።

ከወይዘሮ የሺመቤት ደሬሳና ከአባቱ ከአቶ ደንኪ ሊንጊ በወለጋ ግዛት ጩታ በተባለች መንደር የተወለደው ሰለሞን ደሬሳ በኋላ ከተለያት አሜሪካዊ ባለቤቱ የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበር።

የቀብር ስነስርአቱም ነገ በዚህ ሀገር አቆጣጠር ከቀኑ በ2 ሰአት በሚኒሶታ ከተማ እንደሚከናውን ለማወቅ ተችሏል።