ታዋቂው የባህል ሙዚቃ አቀንቃኝ ድምጻዊ ሀብተሚካኤል ደምሴ ከዚህ አለም በሞት ተለየ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 29/2010)ታዋቂው የባህል ሙዚቃ አቀንቃኝ ድምጻዊ ሀብተሚካኤል ደምሴ በድንገተኛ አደጋ ከዚህ አለም በሞት ተለየ።

ድምጻዊ ሀብተሚካኤል ደምሴ ከዚህ አለም በሞት የተለየው በደረሰበት የመኪና አደጋ ነው።

ሀብተሚካኤል ደምሴ በአዲስ አበባ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አካባቢ ከሚያሽከረክረው መኪናው ወርዶ መንገድ በማቋረጥ ላይ ሳለ በአንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ተገጭቶ ሕይወቱ አልፏል።

አደጋው የደረሰበት ዛሬ ሰኞ ከረፋዱ 4 ሰአት አካባቢ ነው።

ከዚህ አለም የተለየው ድምጻዊ ሀብተሚካኤል ደምሴ በሀገር ባህል ሙዚቃው የሚታወቅ እጅግ ተወዳጅ አርቲስት ነበር።

ድምጻዊ ሀብተሚካኤል የማሲንቆ፣የበገናና የክራር መሳሪያዎችንም በመጫወት ይታወቃል።–ከዚህም ሌላ ሀብተሚካኤል በተለያዩ ቲያትሮችም ላይ በመተወን ይታወቃል።

ከመኪና አደጋው በኋላ የድምጻዊ ሀብተሚካኤልን ሕይወት ለማትረፍ ወደ ጳውሎስ ሆስፒታልና አቤት ሆስፒታል ቢወሰድም በጭንቅላቱ፣በአፍንጫውና በጆሮው  ደም ይፈሰው ስለነበር ሕይወቱን ለማትረፍ አለመቻሉን የአይን እማኞች ተናግረዋል።

ኢሳት በድምጻዊ ሃብተሚካኤል ደምሴ ሞት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቹና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል።