በደቡብ ኦሞ ህወሃት የሚያካሂደውን የመሬት ዝርፊያ መጋለጥ ተከትሎ ሰዎች ታሰሩ

መጋቢት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ህወሃትና ከህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸው የአንድ አካባቢ ተወላጆች፣ ከ98 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዞኑን መሬት ለግብርና በሚል ከተቀራመቱትና መሬቱን አስይዘው ከፍተኛ ብድር መውሰዳቸው ከተጋለጠ በሁዋላ፣ የዞኑ ባለስልጣናት የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችንና ታዋቂ ግለሰቦችን ይዘው በማሰር ከአርበኞችን ግንቦት7 ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት ክስ ለመመስረት በዝግጅት ላይ ናቸው።
የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት ም/ል ሊቀመንበርና የዞኑ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አለማየሁ መኮንን፣ በዞኑ በፖለቲካ ተሳትፎአቸው የሚታወቁት አቶ አብርሃም ብዙነህ እንዲሁም በጅንካ ከሚኖሩ ታዋቂ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ስለሺ ጌታቸው መጋቢት 17 ቀን 2008 ዓም ከተያዙ በሁዋላ ወደ ጅንካ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል።
የእስረኞች ቤት ከማለዳው 12 ሰአት እስከ ረፋዱ 4 ሰአት ድረስ ሲፈተሽ የዋለ ሲሆን፣ ከአቶ አለማየሁ ቤት ከዞኑ የሚመጡ መረጃዎችን የሚመዘግቡበት ማስታወሻ ደብተር፣የራሳቸውና የባለቤታቸው የእጅ/ሞባይል ስልኮች የተወሰዱባቸው ሲሆን የአቶ አብረሃምም የእጅ ስልካቸው ተወስዷል፡፡
በአቶ ዓለማዬሁ ቤት ሰባት የታጠቁ የከተማው ፖሊሶች ለፍተሻ በሚል ተገኝተው የተያዦችን ቤተሰብና የአካባቢውን ነዋሪዎች ሲያሸብሩ መዋላቸውን የአይን ምስክሮች ገልጸዋል።
የእስራቱ መነሻ ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ግንኑነት አላቸው በሚል ጥርጣሬ እንደሆነ ፖሊስ ለፍተሸ ከፍርድ ቤት ካወጣውው ትዕዛዝ ማወቅ መቻሉን የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት ሊቀመንበር አቶ ግርማ በቀለ ገልጸዋል፡፡
በፍተሻ ምንም ነገር አለመገኘቱን ተከትሎ አቶ አለማየሁ ለምን እንታሰራለን ብለው ዛሬ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ የፖሊስ አዛዦች መልስ ሊሰጡ አለመቻላቸውን የገለጹት አቶ ግርማ፣ ምንም እንኳ ሰዎቹ ከተያዙ 48 ሰአታት ያለፋቸው ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
አቶ ግርማ የመንግስት እርምጃ “በዞናችን ውስጥ በሁሉም ህዝብ ዘንድ ስርዓቱ ተቀባይነት ያጣበትና በተለያዩ ቦታዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ማድረግ በመጀመሩ፣ በቃኝ በማለቱ፣ መሬታችንን ለማናውቃቸው ሰዎች እየሰጠ መሆኑ፣ በስኳር ልማት ስም የህዝብን ፍላጎት ግምት ውስጥ ሳያስገባ እያፈናቀለ፣ የሰው ልጅ ከዱር አራዊት አንሶ እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑ ህዝቡ ተቃውሞ እየሰማ በመሆኑ፣ ህዝባዊ እንቅስቃሴውን ለመግታት ከፍርሃትና መደናበር የተነሳ የተወሰደ ነው” ይላሉ።
አቶ ዓለማየሁ ቀደም ብሎ የካቲት 15 እንዲሁም አቶ አብረሃም መጋቢት 03 ታስረው እያንዳናዳቸው የ800 ብር ዋስ ጠርተው መለቀቃቸው ይታወሳል ፡፡ በወቅቱ አርበኞች ግንቦት7 ደቡብ ኦሞ ውስጥ ገብቷልና በማጋለጥ ሂደቱ ውስጥ ተባበሩን ተብለው ተጠይቀው ነበር። ይሁን እንጅ ሁለቱም ተከሳሾች ፣ ስለሚባለው ነገር ምንም መረጃ እንደሌላቸው በመግለጽ ከእስር ተለቀዋል። የህወሃት የመሬት ዝርፊያ ሪፖርት በኢሳት ይፋ ከሆነ ፣ ጥናቱን የሰሩትን ሰዎች አድኖ ለመያዝ እንቅስቃሴ መጀመሩን ኢሳት ቀደም ብሎ መረጃ ደርሶት ነበር።