በአፋር አርብቶ አደሮችና በትግራይ ልዩ ሃይል መካከል በተፈጠረ ግጭት በትንሹ ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 1/2010) በአፋር አርብቶ አደሮችና በትግራይ ልዩ ሃይል መካከል በተፈጠረ ግጭት በትንሹ ዘጠኝ ሰዎች ተገደሉ።

የአፋር የሰብዓዊ መብት ድርጅት ለኢሳት እንዳስታወቀው በመጋሌ ወረዳ ዳንቲ በተባለ አካባቢ ከትላንት ጠዋት ጀምሮ በሁለቱ ወገኖች በጦር መሳሪያ የታገዘ ውጊያ እየተደረገ ነው።

የትግራይ ልዩ ሃይል የፈጸመው ድንገተኛ ወረራ ለግጭቱ መንስዔ መሆኑን የሚገልጸው የአፋር የሰብዓዊ መብት ድርጅት በግጭቱ ከልዩ ሃይሉ ስድስት፡ ከአፋር ደግሞ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

ከተገደሉት ስድስቱ የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት አንደኛው የመከላከያ ሰራዊት አባል መሆኑን በኪሱ በተገኘ መታወቂያ መረጋገጡንም ገልጿል።

ከሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢ ከሚገኘው ከኢሳ ጎሳ ጋር ግጭት መፈጠሩም ታውቋል።

በአፋር ክልል በሶስት ግንባሮች ግጭት ተከስቷል።

በገዋኔ ወረዳ ከኢሳ ጎሳ፣ በጭፍራ ወረዳ ከአማራ፣ በመጋሌ ወርዳ ደግሞ ከትግራይ ልዩ ሃይል ጋር።

የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ፕሬዝዳንት አቶ ገአስ አህመድ ለኢሳት እንደገለጹት የአፋር ህዝብ በታሪኩ እንደዚህ ተደጋጋሚና የማያባራ ግጭት ውስጥ ገብቶ አያውቅም።

የትግራይን መስፋፋት መነሻ ያደረገው የህወሀት መንግስት ወረራ ከአፋር ክልል መሬቶችን ለመውሰድ በሚል የጀመረው ግጭት ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል።

ትላንት በመጋሌ ወረዳ ዳንቲ በተባለው አካባቢ የትግራይ ልዩ ሃይል የፈጸመው ወረራ በአፋር አርብቶ አደሮች በኩል በተወሰደው የመከላከል እርምጃ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉ ታውቋል።

በአፋር ክልል የሚገኙትን ጨውና የፖታሺየም ምርቶችን ለመቆጣጠርና በረጅም ጊዜ እቅድም የታላቋን ትግራይ ህልም እውን ለማድረግ በተጀመረው ጥቃት አካባቢው ሰላም ርቆት እንደሚገኝ ይነገራል።

በመጋሌ ወረዳ እየተካሄደ ባለው ውጊያ ከአፋር አርብቶ አደሮች በኩል ሶስት ሰዎች ሲገደሉ ከትግራይ ልዩ ሃይል ስድስት ታጣቂዎች መገደላቸው ታውቋል። አንደኛው የመከላከያ ሰራዊት አባል እንደሆነ አቶ ገአስ አህመድ ይናገራሉ።

በዚሁ ሳምንት በአፋር ገዋኔ ወረዳ የተጀመረው ግጭት በእስከአሁን ሂደቱ ለበርካቶች ህይወት መጥፋት ምክንያት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በትክክል ግን የሞቱት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ለጊዜው ማወቅ አልተቻለም።

በገዋኔ ወረዳ ከሮማ በተባለ ቀበሌ በተካሄደው የአፋርና የኢሳ ጎሳ ግጭት መሃል የገባው የሶማሌ ልዩ ሃይል ወረራ መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን ልዩ ሃይሉ በአፋሮች ላይ በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት መፈጸሙን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ግጭቱ አሁንም ያልበረደ ሲሆን መከላከያ ሰራዊት በመሃል መግባቱ ታውቋል።

በሌላ በኩል በአማራና በአፋሮች መካከል በጭፍራ ወረዳ ለሳምንታት የዘለቀው ግጭት ለጊዜው ጋብ ያለ መሆኑ ቢገለጽም ዳግም ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት መንገሱ ይነገራል።

በዚሁ ግጭት ከሁለቱም ወገኖች ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን ግጭቱን በመቀስቀስና በማማባስ ረገድ የህወሀት መንግስት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የአፋር የሰብዓዊ መብት ድርጅት አስታውቋል።