በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት በተነሳው ሰደድ እሳት ቢያንስ 11 ሰዎች መሞታቸው ተሰማ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 30/2010) በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት በተነሳው ሰደድ እሳት ቢያንስ 11 ሰዎች ሲሞቱ ከ1500 በላይ ቤቶች ወድመዋል።

ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም የመቃጠልና በጭስ የመታፈን ጉዳት የደረሰባቸው ከ100 በላይ ሰዎችም ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ብሏል ፎክስ ኒውስ በዘገባው።።

በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የተነሳው ሰደድ እሳት የወይን ሀገር በመባል የሚታወቁትን የናፓ፣ሶኖማ፣ዮባና ሜንዶሲኖ አካባቢዎችን ክፉኛ መጉዳቱ ታውቋል።

ከ12 በላይ ሰደድ እሳት በተነሳበትና እሁድ ማታ በጀመረው በዚህ አደጋ እስከ ሰኞ ማታ ድረስ 482 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ያህል ቦታ በሰደድ እሳቱ ተዳርሷል።

ከ20 ሺ በላይ ሰዎችም ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ተገደዋል።

እሳቱ በአካባቢው በሚነፍሰውና በሰአት ከ50 ማይል በላይ በሚጓዘው አውሎ ንፋስ ምክንያት በፍጥነት ሊዛመት መቻሉን የካሊፎርኒያ የደንና የእሳት አደጋ መከላከያ መምሪያ ዳይሬክተር ኬን ፒሞትን ጠቅሶ ሲ ኤን ኤን ዘግቧል።

ዛሬ ማክሰኞ ግን የንፋሱ ፍጥነት ወደ 13 ማይል በሰአት በመቀነሱ የእሳት አደጋ መከላከያ ግብረሃይሉ እፎይታ ማግኘቱ ታውቋል።

የሰደድ እሳቱ በተለይ 175 ሺ ነዋሪዎች ያሏትን የሳንታ ሮሳ ከተማን ሙሉ በሙሉ በማውደሙ ቤቶችና ተሽከርካሪዎች ወደ ከሰልና አመድነት ተቀይረዋል።

እስካሁን በከተማዋ 7 ሰዎች ሲሞቱ ቁጥሩ ግን ከዚህም በላይ ከፍ ሊል እንደሚችል የከተማዋ የፖሊስ አዛዥ ተናግረዋል።

ፋውንቴን ግሩቭ ኢን የተባለውና ባለ 124 ክፍል ሆቴል፣የከብቶች ማድለቢያ እንዲሁም በከተማው የሚገኘው የባህል ማዕከል የመማሪያ ክፍሎች በእሳቱ ከወደሙት መካከል ናቸው።

እኔ እድለኛ ነኝ ቤቴና ቤተሰቤ ተርፏል ከተማዬ ግን አልተረፈችም ብለዋል የሳንታ ሮሳ ከንቲባ ክሪስ ኮርሲ።

ሰደድ እሳቱ በተነሳባቸው አካባቢዎች የነበሩ የወይን ተክሎችና መጥመቂያዎች ወድመዋል።

ሃይለኛ ንፋስና ደረቅ የአየር ጸባይ ለእሳቱ መነሳትና መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ የተያዘው የጥቅምት ወር ደግሞ የሰደድ እሳት በብዛት የሚነሳበት ወቅት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።