በሰሜን ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ አዲስ ውጥረት ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 9/2010) በሰሜን ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ አዲስ ውጥረት መቀስቀሱ ተሰማ።

ባለፈው ዕሁድ የተሰጠውን ህዝበውሳኔ ተከትሎ የተቀሰቀሰው ውጥረት እስከአሁን የአራት ሰዎችን ህይወት ማጥፋቱ ተሰምቷል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመንግስት ሰራዊትም ወደ አካባቢው መግባቱ ታውቋል።

ያለህዝብ ይሁንታ ቀደም ብለው የተካለሉት 42ቱ ቀበሌዎች ላይ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ከህዝብ ግፊት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት ግጭት መፈጠሩ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።

በህዝብ ተቃውሞ ውድቅ በተደረጉት 4 ቀበሌዎች ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግባቸው በህወሀት መንግስት በኩል እንቅስቃሴ መጀመሩ ለግጭቱ መንስዔ እንደሆነ የአካባቢው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

በሰሜን ጎንደር የቅማንትና የአማራን ማህበረሰብ ለመለየት በሚል የተካሄደውን ሕዝበ ውሳኔ ተከትሎ ግጭት እያገረሸ ይገኛል።

ምክንያቱ ደግሞ የቅማንት ኮሚቴ አባላት የሚባሉና በሕወሃት የሚመሩ ታጣቂዎች የምርጫው ውጤት ለምን አቅጣጫውን ቀየረ በሚል ሕዝቡን በማስጨነቃቸው ነው ተብሏል።

የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት ሕወሃት በአካባቢው ከተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ሊማር አልቻለም።

እንዲያውም በአካባቢው ግጭት በመፍጠር ሕዝበ ውሳኔ ባልተካሄደባቸው 4ቱ የቅማንትና የአማራ ሕዝብ የጋራ መኖሪያዎች ድምጽ መሰጠት አለበት በሚል ሕዝቡን ለምርጫ ማስገደድ ጀምሯል ነው የተባለው።

በ12ቱ ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔው ይካሄዳል ከተባለ በኋላ በ4ቱ ቀበሌዎች የአካባቢው ሕብረተሰብ አንመረጥም በሚል ለምዝገባ ፍቃደኛ አልሆነም ነበር።

እነዚሁም ቀበሌዎች ለዛ፣አወራረዶ፣አደዘና ገለድባ ናቸው።

እናም ከፌደራል ፣ከክልልና ከዞን የተላኩ ካድሬዎች የአካባቢውን ሕዝብ ሰብስበው ለዘመናት ሲጠየቅ የነበረው የቅማንት ማንነት ጥያቄ በዚህ መልኩ ሊደፈን አይገባም በማለት በዛቻ ቅስቀሳ ጀምረዋል።

ይህንኑ ተከትሎም በነዚሁ ቀበሌዎች ግጭት መቀስቀሱንና 4 ሰዎች ሌሊቱን መገደላቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

የቅማንት ማህበረሰብ አሸንፏል የተባለበት ኳርበር ኮዛ ቀበሌም ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ሕዝቡ ተቃውሞ አሰምቷል።

በዚህችው ቀበሌ 1148 ቅማንት ነን በሚል 2426 ደግሞ አማራ ነን ብለው ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ ቢሆንም ውጤቱ የተገላቢጦች መሆኑ ብዙዎችን አስገርሟል።

ብዙዎቹ አማራ ነን የሚሉት ድምጻችን የት ገባ እያሉ እየጠየቁ መሆናቸውም ተነግሯል።

ይህ ብቻ አይደለም በሕወሃት/ብአዴን ውሳኔ 42 ቀበሌዎች በቅማንት ስር ይተዳደራሉ ተብሎ ቀደሞ መወሰኑም ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል።

በእነዚህም አካባቢዎች መወሰን ያለበት ሕዝቡ እንጂ አገዛዙ አይደለም ባይ ናቸው።ቅማንትና አማራ አንለይም የሚሉት የጎንደር ነዋሪዎች።