በሊቢያ የታገቱ 260 ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ሁኔታ እንዳሳሰበው አለም አቀፍ የስደተኞች ተቋም ገለጸ

ኢሳት (ሰኔ 8 ፥ 2009)

በሊቢያ በህገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችና በወንጀለኛ ቡድኖች ተይዘው የሚገኙ ወደ 260 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ስደተኞች ሁኔታ እጅግ እንዳሳሰበው አለም አቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM) አስታወቀ። በእነዚህ ቡድኖች ተይዘው የሚገኙት ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውን ስደተኞች መካከል ብዛት ያላቸው ህጻናት እንደሚገኙበት ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።  

ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እየተሰራጨ የሚኘውን ቪዲዮ ዋቢ በማድረግ ስጋቱን የገለጸው የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM)፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰውነታቸው የተጎሳቆለና ሰቆቃ የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን በአንድ ክፍል ውስጥ ታስረው መታየታቸው ገልጿል። ከኢትዮጵያውያንና ከሶማሊያውያን በተጨማሪም የሌላ አገር ዜጎችም ሊገኙበት እንደሚችል በድርጅቱ ድረገጽ ላይ የወጣው ዘገባ ያመለክታል።

በቪዲዮ የሚታዩት ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና ሰቆቃ እንደደረሰባቸው ያመለከተው ድርጅቱ፣ በድብደባ ብዛት ጥርሳቸው የወለቀ፣ እጃቸው የተሰበረ እንዳሉበት ገልጾ፣ ስደተኞቹ ለብዙ ቀናት ምግብ እንዳላገኙ መግለጻቸውን አትቷል።

ሴት ስደተኞች በተለየ ክፍል እንዲታሰሩ መደረጉን የገለጸው የአለም አቀፍ ስደተኞች ሪፖርት፣ ከወንዶቹ በተለየ መልኩ ጾታዊና አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸው ሊሆን ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል።

ወንጀለኛ ድርጅቶቹ የታጋች ወላጆችና ዘመዶቻቸው ከ 8ሺ እስከ 10 ሺ ዶላር ካልከፈሏቸው ታጋቾቹ እንደሚገደሉ የሚገልጹ አጫጭር ቪዲዮዎችን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ቀድቶ በመላክ ገንዘብ እንደሚቀበሉ ተገልጿል።

ታጋች ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ስደተኞች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲያደርጉ የነበሩት ግንኙነት ለረጅም ጊዜ የተቋረጠ ሲሆን፣ ስደተኞቹ የተያዙበት ቦታ በእርግጠኝነት አለመታወቁ ተገልጿል። “ለአንድ አመት እዚህ ነበርኩ፣ በየቀኑ ተደብድቤያለሁ፣ ምግብ አላገኝም፣ ሰውነቴም ቆስሏል” ያለው አንድ ሶማሊያዊ ለአራት ቀናት ምግብ ባይበላም ያስመረረው ግን በየቀኑ የሚደርስበት ድብደባ እንደሆነ ምሬቱን ገልጿል።

በሊቢያ የሚገኙ የሰው አዘዋዋሪዎችና አፋኝ ቡድኖች በረሃብ የተጎዳን አንድ ወጣት ታጋች ቤተሰቦቹ የገንዘብ ክፍያ ባለመፈጸማቸው ትልቅ ድንጋይ በማሸከም መቀጣጫ እንዳደረጉት በድርጅቱ ድረገጽ የወጣው ሪፖርት አጋልጧል። ለ11 ወር የታሰረው ይኸው ወጣት በድብደባ ብዛት ጥርሱ እንደወለቀና እጁ የተሰበረ መሆኑን ገልጾ፣ ይህንን ያደረጉት የተጠየቀውን 8 ሺ ዶላር ቤተሰቡ መክፈል ባለመቻሉ ነው ብሏል።

ለአንድ አመት የታሰረውና በየቀኑ የድብደባ ጥቃት ይፈጸምብኛል ያለው ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ እርዳታ ተደርጎለት ወደ አገሩ መመለስ እንደሚፈልግ ተማጽኖ አቅርቧል። ለአራት ቀን ምግብ እንዳላገኘና፣ በድብደባ ብዛት ሰውነቱ እንደቆሰለም ገልጿል ።

አለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) በድረገጹ እንዳስታወቀው፣ ሶማሊያውያንና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መደብደባቸውና ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው ማየት ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረበት አስታውቋል። የአለም አቀፍ ስደተኞች የአስቸኳይ ጊዜ ኦፕሬሽን መምሪያ ዳይሬተር የሆኑት ሞሃመድ አብዲከር፣ በሊቢያ የሚገኙ የወንጀለኛ ቡድኖች ገንዘብ ከቤተሰቦቻቸው ለማግኘት ሲሉ በታጋዮች ላይ አሰቃቂ ድርጊት መፈጸማቸውን በጥብቅ ያወግዛል ብለዋል።

ችግሩ አለም አቀፍ ይዘት ያለው ነው ያሉት ሚስተር ሞሃመድ አብዲከር፣ የወንጀለኛ ቡድኖች የማህበራዊ መገኛኛ ብዙሃንን በመጠቀም ይህንን እኩይ ድርጊታቸውን ለማስፋፋት፣ ስደተኞችንና ቤተሰቦቻቸውን ለመበዝበዝ ይጠቀሙበታል ሲሉ ኮንነዋል። የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ባለቤቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ የማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው እንዲህ አይነት ሰቆቃዎችን እንዳይተላለፉና እንዳይሰራጩ ሊያስቆሙ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሊቢያ የሚገኙ የህገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች በስደተኞችና ግጭትን በመሸሽ ወደ ሌላ አገር በሚሸሹ ሰዎች ላይ የሚያደርሱት ዕኩይ ድርጊት መጨረሻ የለውም ሲሉ በተባበሩት መንግስታት የመካከለኛ ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ የስደተኞች ድርጅት ዳይሬክተር አሚን አዋድ ገለጸዋል።

UNHCR በሊቢያ የታገቱት ኢትዮጵያውያንና ሶማሊያውያን ከሊቢያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በመተባበር በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል። በወንጀለኛ የሊቢያ ቡድኖች ተቀርጾ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የተለቀቀውንና እየተሰራጨ የሚገኘውን አሰቃቂ የቪዲዮ ምስልም አውግዟል።

ከምስራቅ አፍሪካ ወደ ሊቢያ የሚጓዙ ስደተኞች ከሱዳን ጋር በሚዋሰን ራይባና በሚባል አካባቢ በተደጋጋሚ እገታ እንደሚደርስባቸው ተገልጿል። የሊቢያ ባለስልጣናትም ችግሩን በደምብ እንደሚያውቁትና የስደተኞች ድርጅትም በሊቢያ የመንግስት ባለስልጣናትን ላይ ግፊት እንደሚያደርግ አስታውቋል። ታጋቾቹ ከተለቀቁ ድርጅቱ  ወደ አገራቸው የሚመለሱበት የትራንስፖርት፣ የህክምና ወጪና ሌሎች ወጪዎችን እንደሚሸፍን ገልጿል።