ሰመጉ በጋምቤላ ለጠፋው የሰው ህይወትና ለወደመው ንብረት መንግስትን ተጠያቄ አደረገ

ሚያዚያ ፲፱(አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ባወጣው ጋዜጣው መግለጫ፣ ከ200 በላይ ንጹሃን ዜጎች ለተገደሉበት ከ100 በላይ ዜጎች ለቆሰሉበትና በርካታ ህጻናትና ሴቶች ተጠልፈው ለተወሰዱበት ድርጊት ፣ መንግስትን ግንባር ቀደም ተጠያቂ አድርጓል።
ከደቡብ ሱዳን የሚመጡ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ግድያና ዝርፊያ እየፈጸሙ መሆኑ እየታወቀ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውንና ንብረታቸውን የሚከላከሉበትን መሳሪአ በመንግስት እንዲፈቱ መደረጉ አንድ ጥፋት መሆኑን የጠቀሰው ሰመጉ፣ የክልሉ ፖሊስና ልዩ ሃይል አባላት ትጥቅ እንዲፈቱ መደረጉ ድርጊቱን መከላከል እንዳይቻል በማድረጉ ሌላ ጥፋት ተሰርቷል ብሎአል።
ህገወጥ ድርጊቱ ከመፈጸሙ አስቀድሞ ነዋሪዎችና ባለስልጣናት የድረሱልን ጥበቃ ይደረግልን ቢሉም በመንገስት በኩል ተገቢውናነ ፈጣን ምላሽ ባለማግነታቸው አሁን ለደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ሌላው ምክንያት መሆኑን ጠቅሷል።
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ ቁጥራቸው ከ63 በላይ ሰዎች በኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር ተፈጸመ በተባለ ጥቃት ህይወታቸውን ሲያቱ፣ በትግራይና አፋር ክልሎች ጠረፋማ አካባቢዎች ዜጎች በየጊዜው እየታፈኑ ሲወሰዱ፣ መንግስት ችላ ማለቱንና ትምህርት አለመውሰዱ፣ በጋምቤላ ለደረሰው አሰቃቂ ድርጊት የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል ብሎአለ።
በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት በኦሮሚያ ክልል የገጠመውና ለበርካታ ሰዎች መሞት ምክንያት የሆነውን ቀውስ የኦፌኮ ተቀዳሚ ም/ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ በቀለ ገርባ ጨምሮ በ22 ተከሳሾች ላይ መለጠፉ በአዲስ አበባ ከተማ አነጋጋሪ ጉዳይ መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል።
አቃቤ ህግ ትላንት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በንባብ ባቀረበው ክስ መሰረት በኦሮሚያው ተቃውሞ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውን ፣በ122 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል አደጋ መድረሱን፣ 122 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ አድርጎአል።
ጠ/ሚኒስትር ሀይለማርያም በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው ተቃውሞ መነሻው ራሱ ኦህዴድ/ኢህአዴግ መሆኑን በይፋ ከማመን አልፈው በጽ/ቤታቸው ተገኝተው ላነጋገሩዋቸው አባገዳዎች ለተጎዱ ወገኖች መንግስት ካሳ እንደሚሰጥ የተናገሩ ቢሆንም፣ የተቃውሞው አንቀሳቃሾች እነ አቶ በቀለ ገርባ ሆነው መቅረባቸው አነጋጋሪ ሆኖአል።
ጠ/ሚኒስትሩ “በኦሮምያ የተነሳው ተቃውሞ የመልካም አስተዳደር ችግርና ስርአጥነት የፈጠሩት ነው፣ ጥፋተኞች ነን” ብለው በአደባባይ ተናግረው ባለበት ሁኔታ ፣ ተጠያቂ ያልሆኑ ግለሰቦችን አስሮ ፣ ለደረሰው ጥፋት ሁሉ ተጠያቂዎች ናቸው ብሎ ክስ መመስረቱ፣ ተቃውሞውን ለማብረድ መንግስት የተጠቀመበት ስልት ሊሆን እንደሚችል፣ ካልሆነም የፈለገውን እየወነጀለ የሚያስር ከአቶ ሃይለማርያም ውጭ ያለ ሌላ ስልጣን ያለው አካል መኖሩን ያሳያል በማለት ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ሰዎች ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ሰዎች የተገደሉት መንግስት ባሰማራቸው ታጣቂዎች እንጂ በእነበቀለ ገርባ አይደለም ያለው አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ወንጀለኞቹ ሳይጠየቁ የተቃዋሚ ፖርቲ አባላትን ማሳደድና በእስራት ማሰቃየት እውነቱን ሊሸፍነው አይችልም ብለዋል። እነአቶ በቀለ የቀረበባቸውን የክስ መቃወሚያቸውን ግንቦት 3 እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።
በሌላ የፍርድ ቤት ዜና ደግሞ የቀድሞው የጋንቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩትና ከደቡብ ሱዳን ታግተው ወደ ኢትዮጵያ የተወሰዱት አቶ ኦኬሎ አኳይን ጨምሮ ሌሎች በተመሳሳይ ወንጀል የተከሰሱት ፍርድ ቤት የእስር ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል።
ተከሳሾቹ አቶ ኦኬሎ አኳይ፣ ዴቪድ ኡጁሉ፣ ኡቻን ኦፔይ፣ ኡማን ኝክየው፣ ኡጁሉ ቻም፣ አታካ ኡዋር እና ኡባንግ ኡመድ ሲሆኑ ፍርድ ቤቱም በአንደኛ ተከሳሽ አቶ ኦኬሎ አኳይ እና ሁለተኛው ተከሳሽ አቶ ዴቪድ ኡጁሉ ላይ የ9 አመት ጽኑ እስራት ሲወስን፣ ከ3ኛ እስከ 7ኛ ያሉት ሌሎች ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው በሰባት አመት ጽኑ እስራት እዲቀጡ ብሎአል።
አቶ ኦኬሎ የቀረበባቸውን ክሶች በሙሉ ቢቃወሙም፣ ፍርድ ቤቱ ግን የክስ መቃወሚያቸውን ሳይቀበላቸው ቀርቷል።