ህዝቡ ስለወልቃይት ማንነት የተጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ተደረገ

(ኢሳት ዜና–ጳጉሜ 2/2009)በግጨው የድንበር ወሰን ላይ ከስምምነት ደርሰናል በሚል በብአዴንና ህውሀት መሪዎች በተሰጠው መግለጫ ህዝቡ ሳይዘናጋ ስለወልቃይት ማንነት የተጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ተደረገ።

ልሳነ ግፉአን የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ማህበረሰብ ለኢሳት እንደገለጸው የትግራይ ገዢ ቡድን አሸናፊ ሆኖ የወጣበትን ስምምነት የአማራውም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሊያወግዘው ይገባል።

ትላንት የሁለቱ ድርጅቶች መሪዎች አጨቃጭቆናል ባሉት የግጨው የወሰን ጉዳይ ላይ ስምምነት መድረሳቸውን ያስታወቁ ሲሆን ለጸረ ሰላም ሀይሎች አፍራሽ ተግባር በር የዘጋ ስምምነት ሲሉም አወድሰውታል።

ከ1983 በፊት በጎንደር ክፍለሀገር በወገራ አውራጃ ስር የነበረው የግጨው ወሰን ህወሀት ስልጣን ከያዘ በኋላ ወደትግራይ ክልል መጠቃለሉ ይታወሳል።

ሁለቱም ቡድኖች በለስ ቀናን ይላሉ። በየፊናቸው የድል ዜና ለህዝብ ይፋ አድርገዋል -ትላንት።

የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብአዴን የግጨው መሬት ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ለአማራ ተሰጠ ሲል ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀትም ግጨውን ጨምሮ የትግራይ ቦታዎች የነበሩ የይገባኛል ጥያቄዎች በማያወላዳ መልኩ የትግራይ ክልል መሆናቸው ተረጋግጧል ሲል በኮሚኒኬሽን ቢሮ በኩል ባወጣው መግለጫ ላይ ተገልጿል።

የሁለቱ ክልሎች ፕሬዝዳንቶች የግጨው ጉዳይ ተፈቷል ያሉበትን ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ እንደተናገሩት ከእንግዲህ ሰላም የሚያሳጣ የወሰን ጭቅጭቅ አይኖርም።
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስምምነቱ ለጸረ ድህነቱ ዘመቻ ጉልበት የሚሰጠን ነው ሲሉ አቶ አባይ ወልዱ ደግሞ ጠላቶቻችን አገኘነው ያሉትን ክፍተት የዘጋ ስምምነት በማለት አወድሰውታል።

ብአዴንና ህውሀት ተስማማን ያሉበት የወሰን ጉዳይ በህዝብ ዘንድ ብዙም ትኩረት አላገኘም።

ህወሀት ወደስልጣን ከመውጣቱ በፊት በጎንደር ክፍለሀገር ስር የነበረውን ቦታ በሃይል በመያዝና ከትግራይ ነዋሪዎችን በማምጣት ካሰፈረ በኋላ ጠገዴን፡ ጸገዴ በሚል የፊደል ለውጥ አድርጎ የይገባኛል ጥያቄ ያነሳበትን አሁን በስምምነት ስም ህጋዊ ማድረጉን የሚገልጹ ወገኖች አሸናፊው ህወሀት በሆነበት ስምምነት ለአማራው እንደድል መነገሩ የሚያሳፍር ተግባር ነው በማለትም ያጣጥሉታል።

የልሳነ ግፉአን የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ማህበረሰብ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቻላቸው አባይ እንደሚሉት በዚህ ስምምነት የአማራው ህዝብ ያገኘው ነገር የለም። የአባይ ወልዱ ቡድን እንጂ።

የግጨው የወሰን ጉዳይ ከስምምነት ተደረሰ መባሉ ዋናውን የወልቃይት የማንነት ጥያቄን ለመጨፍለቅ የተወሰደ የማዘናጊያ እርምጃ ነው የሚሉት አቶ ቻላቸው፡ የወልቃይት ጥያቄ የሚፈታው ከህወሀት በኋላ እንጂ ህወሀት እያለ የማይታሰብ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

ትላንት በሁለቱ ድርጅቶች ተደረሰ በተባለው ስምምነት ላይ የትግራይ ኮሚኒኬሽን ቢሮ እንደገለጸው ጥያቄው የአማራ ህዝብ ጥያቄም እንዳልሆነ ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ከስምምነት ላይ ደርሰዋል በማለት መግለጹ የወልቃይት ጥያቄን ህወሃትም እንደማይቀበለው፣ ብአዴንም እንደማይጠይቅ በግልጽ መልዕክት የተላለፈበት እንደሆነም ይነገራል።

ህዝቡ በህወሀት ማደናገሪያና በብአዴን እጅ መስጠት ሳይዘናጋ ትግሉን እንዲቀጥል ጥሪ ያደረጉት የልሳነ ግፉአን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቻላቸው አባይ፡ በህወሀት በኩል ጎንደርን ለማዳከም የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ ጥቃት ለመመከት ከምንግዜውም በላይ ነቅቶ እንዲጠብቅም መልዕክት አስተላልፈዋል።